ሌላ ሰው….. የሃገራችን የስነ ልቦና መጽሃፍት ጅማሬ

                         ˝ሁሉም ሰው ሌላ ሰው ነው…… ሌላውም ሰው እንደኛው ሰው ነውና፡፡˝

በቤተልሄም ሲሳይ
በዶክተር ምህረት ደበበ የተጻፈው ሌላ ሰው የተሰኘው መጽሃፍ ሰኔ 2007 ለንባብ በቅቷል ፤ ስድስት ምእራፎች እንዲሁም 49 ክፍሎች  እና 451 የገጽ ብዛት ያሉት ሲሆን ፤ በአእምሮ ጤንነት  እና ስነ ልቦና ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ ይህ መፅሐፍ ስነ ልቦናንና ስብዕናን የሚፈትሹ ማህበረሰባዊና ግለሰባዊ አንኳር እይታዎችን እንዲሁም ረቂቅ የአዕምሮ እክሎችን ይዳስሳል፡፡ ሌላ ሰው፣ የደራሲው ሁለተኛ ስራ የሆነውን መጽሃፍ በትንሹም ቢሆን ለመዳሰስ ወደድኩ፤ እነሆ፡፡
ሌላ ሰው በማራኪ አተራረክ ችግሮቻችንን ነቅሶ ያሳየናል፡፡ ትንሽ ያልነውን ችግር አጠብድሎ እንድንታዘብ ሲያደርገን ትልቅ አድርገን የወሰድናቸውን አንዳንድ አጉል ማህበረሰባዊ ባህሎችና እክሎች አሳንሶና አኮስሶ ያስገርመናል፡፡ ያሳፍረናል፡፡ ዛሬ ለእኛነታችን መሰረት የሆኑ ያለፉና የተረሱ፣ የበሰበሱ ጨለማ ትዝታዎቻችን ምን ያክል ሃላፊነትእንደሚወስዱ ያስረዳናል፡፡ ራሳችንን በሌላሰው መነጽር ውስጥ አድገን እንድናስተውል፤ አስተውለንም እግሮቻችንን በሌላ ሰው ጫማ አጫምተን ወደፊት እንድንራመድ ያደርገናል፡፡ ሌላ ሰው እንግዲህ እንዲህ እያለ በተረብ አዋዝቶ እያጫወተ…. እያጫወተ…. እስከመጨረሻው ምእራፍ አብሮን ይጓዛል፡፡   
   የመጽሃፉ የፊት ገጽ ሽፋን እያንዳንዱ ሰው በውስጡ ሌላ ሰው ይዞ እንደሚዞር ይነግረናል፡፡ ሲደሰቱ የምናውቃቸው ሰዎች ሲያዝኑ ደግሞ ሌላ ሰው መሆናቸውን፤ ሲያገኙ የምናውቃቸው ስብዕናዎች በማጣት እንደሚቀየሩ፣ በአጠቃላይ ሰዎች የማህበረሰቡ፣ ያለፈ ህይወታቸው ያሳረፈባቸው ጠባሳ እና የአካባቢያቸው ድምር ውጤት መሆናቸውን በጥልቀት ያሳየናል፡፡
ይህ በአእምሮ ጤንነት ዙሪያ የሚያተኩረው ረጅም ልብ ወለድ በውስጡ ከ አስር ያልበለጡ ዋና ዋና ገጸ-ባህርያትን አሳትፏል፡፡ደራሲው እኛኑ የሚመስሉንና ከሁላችን የለት ተእለት ኑሮ ጋር ቁርኝት ያላቸው ገጸ-ባህርያትን ለመሳል ሞክሯል፡፡  ዋና ገጸ-ባህሪው ˝ሌላ ሰው˝ በስራው የአእምሮ ስፔሺያሊስት ሲሆን ከባለቤቱ እና ከ ሁለት ልጆቹ ጋር ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ዋና ገጸ-ባህው ኢትዮጵያ ውስጥ የበጎ ፈቀደኝነት ስራዎችን ሲሰራ በቆየባቸው ጊዜያት ሀገሪቷ ውስጥ በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚገኘው የአስተሳሰብና የአእምሮ ጤንነት ችግር ስላሳሰበውና ዘላቂ የሆነ እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች እንዳሉ በመገንዘቡ አሜሪካ ያለውን ህይወት ትቶ እዚሁ በሙያው እንዲያገለግል ሆኗል፡፡ ሌላ ሰው ለአመታት ሲፈልገው የነበረውንና ተለይቶት የኖረውን ምስጢር ከተቆለፈበት ፈልቅቆ ለማውጣት እና በዛ መሃል ደግሞ ቤቱን ከመፍረስ ለማዳን ሲታገል እናየዋለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህይወቱንና የሰጠለት ስራው በገጸ-ባህሪያት የአስተሳሰብ ችግርና የማስተዋል ማጣት ሳቢያ ምን ያክል እንደተናጋ ይተርክልናል፡፡ በህይወቱ የሚገጥሙትን ተስፋ አስቆራጭ እና እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችና መሰናክሎች ጥሶ እነዴት ወደ ወዲያኛው የከፍታ ጫፍ እንደሚሻገር አሳይቶናል፡፡
 እንግዲህ በዚህ ዋና ገጸ-ባህ በኩል ደራሲው እያንዳንዱ ሰው በድርብርብ ማንነት የተለበጠ ስውር ማንነት ያለው ሌላ ሰው ነው ሲል ያስረምረናል፡፡የተለያዩ ሃገራዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ግላዊ አጀንዳዎችን እየዳሰሰ ያልፋል፡፡ ከነዛም መካከል የተወሰኑትን በአጭሩ እንመልከት፡፡
በሆስፒታሎቻችን ላይ የሚታየው ዝርክርክነትና ግዴለሽ አሰራር በመጽሃፉ ውስጥ ከተጠቀሱት መሃከል ይገኝበታል፡፡ ለምሳሌ የጤና ተቛማት ራሳቸው ለአእምሮ ህሙማን ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት ፣ ከአማኑኤል ለሚመጡ ታካሚዎች የሚሰጡት ግዴለሽ የህክምና አገልግሎትና መድሎ የሞላበት አሰራር ህሙማኑን እስከሞት ድረስ ዋጋ እንደሚያሰከፍላቸው ያሳያል፡፡
˝ማንን ትከሳለህ ሌላሰው? ሆስፒታሉን… ሃኪሚቹን… ነርሶቹን… ዘበኞቹን… የጽዳት ሰራተኛዋን… ጤና ጥበቃን… ማንን? ….ደግና ሰው አክባሪ ባህል እየተባለ ቢለፈለፍም እወነቱ ግን ህሊና የሌለው ጨካኝና ለሰው ዋጋ ደንታ የማይሰጠው  ሰው ነው የሚበዛው፡፡…. አእምሮአቸውን በታመሙ ሰዎች ላይ የጤና ባለሙያዎች እንኩዋን ሳይቀሩ ለምምድነው እንዲህ የሚጨክኑት?  ̀አሁን ዝናሽ የአእምሮ ህመምተኛ ባትሆንና ገንዘብ ያላት የተማረች ነብሰ ጡር ብትሆን የጥቁር አንበሳ ተረኛ ዶክተር ሳያያት በግዴለሽነት ይመልሳት ነበር?፡፡˝
 ሌላው፣ ህብረተሰቡ ለሴቶች ያለው አመለካከት ነው፡፡ በሴት የዩንቨርሰቲ ተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ትንኮሳዎች፣ በዚህም ሳቢያ በሚደርስባቸው የስነ ልቦና ቀውስ፤ ተስፋ ማጣት እና ፍርሃት እራሳቸውን እስከ ማጥፋት፣ ትምህርታቸውን እስከማቁዋረጥ የሚያደርሳቸው መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህም በቤተሰቦቻቸው፣ በራሳቸውና በማህበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ሴቶች በየመንገዱ ከተቃራኒ ጾታ ለሚደርስባቸው ትንኮሳ እና ለከፋ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠታቸውና የበዛ ዝምታቸው ለዚህ ቀውስ እንደዳረገ ማሳያ ነው፡፡
ዘነበወርቅ አካባቢ ስለሚኖሩ ሰዎች ደግሞ እጅግ ልብን በሚነካ መልኩ ይተርክልናል፡፡ በእውነቱ የራሳችንንና የነርሱን ህይወት አስተያያተን እኛ በገነት ነው የምንኖረው ብለን ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ቤቶቹ ከመቃብር በላይ በመሰራታቸው ከቀን ወደ ቀን ወደ ውስጥ እየዘቀጡ መምጣታቸው ማንም ሰው እነርሱን አስቡዋቸው እንደማያውቅ ማሳያ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂ መሆናቸው ከሰው ዘር ተለይተው ምድራዊ ገሃነው የሆነ ኑሮ እንዲኖሩ አድርጉዋቸዋል፡፡  
˝አዲስ አበባ የማታውቃቸውና እሷን የማይመስሉ ሌላ አይነት ሰዎች በሌላ ሰፈር እንደሚኖሩ እስካሁን አለማወቛ አስደንግጧል፡፡…… ቆሼና ዘነበወርቅ የአንድ ሰፈር ሁለት ስሞች ናቸው፡፡ …..ዘነበወርቅ፣ ከአፈሩ ወርቅ ባይታፈስም ከወርቅ ይልቅ የከበሩ እንደከዋክብት የሚያበሩት የዝናሽ ልጆችና ሰፈሩ ውስጥ የሚርመሰመሱት ሌሎች ህጻናት ታዩዋት፡፡ ወስ ሚሊዮን ዶላር አፍስሶ ከድንጋይ መሃል ወርቅ ስሳል፡፡ እዚሁ ከተማ መሃል የፈሰሱት ህያዋን ወርቆች ላይ ግን የቤትና የሆቴሉ ቆሻሻ ይደፋባቸዋል፡፡……˝
ታሪኩ በኢትዮጽያ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች እንዲሁም በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች  እየተዘዋወረ ይተርካል፡፡ ይህም ኢትዮጽያ ውስጥ ያለ ሃገርኛ አንባቢ አሜሪካን በትንሹም ቢሆም እንዲያውቅ ይረዳዋል፡፡ በተዘዋዋሪ አሜሪካ ውስጥ ለበርካታ አመታት የቆየ ኢትዮጵያዊ አንባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ በትንሽ መነጽር እንዲያይ ያግዘዋል፡፡
ዶክተር ምህረት በሙያው የአእምሮ ስፔሻሊሰት ሲሆን በአሜሪካና በኢትዮጵያ በሙያው እያለገለ ይገኛል፡፡ የደራሲው ቀደምት ስራ የሆነው የተቆለፈበት ቁልፍ የተሰኘው ረጅም ልብ ወለድ ደግሞ በተመሳሳይ በአስተሰሳብ ለውጥ ዙሪያ ያተኩራል፡፡

ሌላሰው እነዚህንና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን አካቶ በየሁላችንም ጓዳ ገብቶ ይመረምራል፡፡ ራሳችንን በብዙ እንድንፈትሽ ያደርገናል፡፡ እኔ ይህን ያክል ስለ መጽሃፉ ካልኩ ቀሪውን የቤት ስራ ለአንባቢው ተውኩ፡፡ 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አራቱ መንገደኞች