ሻቃ በቀለ ወያ

«አላስኬድም አለኝ ጣሊያን በመንገዱ
  ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ፡፡´´
ኢትዮጵያ ውስጥ በየዘመናቱ ጀግኖች ይፈጠራሉ፤ለሃገራቸውም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ሲሰሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ከየትኞቹም ጀግኖች በላይ ግን የአርበኞች ትግልና ውጤት ጎልቶ ይታያል፡፡ምክንያቱም ደግሞ አርበኞች ህይወታቸውን ሰውተው ባይታገሉና ከአረመኔው የፋሽስት ጦር ባይከላከሉ ኖሮ ከነሱ ወዲያ የመጡት ሀገር ወዳድ ጀግኖች ባልተፈጠሩ፤ቢፈጠሩም ባልጀገኑ ነበር፡፡ለሀገራቸው ነፃነት ለህይወታቸው ሳይሳሱ በፍፁም ጀግንነት ከታገሉ የምንጊዜም ጀግኖች አርበኞቻችን መካከል የደጃዝማች በቀለ ወያን ታሪክ እንዲህ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
 በደቡብ ሸዋ ሶዶ ውስጥ ልዩ መጠሪያው ጎጌቲ ሲብስቶ በሚባል መንደር የሚኖሩት አቶ ወያ ኦብሴና ወይዘሮ ብርቄ ጂሎ ጎዳና ነሀሴ 21 ቀን 1902 ዓ.ም የአብራካቸውን ክፋይ አገኙ፡፡ስሙንም በቀለ ብለው ሰየሙ፡፡በቀለ ካደጉ በኋላ አማርኛን መማር እንዳለባቸው ያመኑት ቤተሰቦቻቸው መምህር ተቀጥሮላቸው ቤታቸው ውስጥ አማርኛን ተምረው ለማጠናቀቅ በቁ፡፡እድሜያቸው 16 ሲሆንም ቤተሰብ በቀለ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ከአጎታቸው ደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪ ጋር እንዲኖሩ ወሰኑ፡፡ወደ አዲስ አበባም ሄደው የደጃዝማች ገብረማሪያምን ቀልብ በስነ-ስርዓት አክባሪነት፤በቅንነትና ጨዋነት፤በእርጋታቸው ና በአስተውሎ መተግበራቸው ለመሳብ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡
ደጃዝማች በቀለ ወያ የመጀመሪያ ማዕረጋቸው ‹‹ሻቃ››የሚል ሲሆን ያገኙትም አጎታቸው ደጃዝማች ገብረማሪያም የሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ማዕረጉም በረዳትነትና የውትድርናና የአስተዳደር ስራ እንዲሰሩ አድርጓቸዋል፡፡አጎታቸው በተሾሙበት የስልጣን እርከን ስር ሁሉ የሚሰሩት ሻቃ በቀለ፤አጎታቸው በ1927 የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ሆነው በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው ሲሾሙ፤አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው ለአንድ አመት ያህል የታንክ መስበሪያ መሳሪያ አጠቃቀምን ለማጥናት ቻሉ፡፡
አረመኔው የፋሽስት ጦር ሀገራችንን ለመውረር ሲመጣ በደጃዝማች ገብረማሪያም ስር የተሰለፈውን ጦር በመምራት ከንጉሰ ነገስቱ በሲዳሞ በኩል እየተጠቃ የነበረውን ጦር እንዲያግዙ ትዕዛዝ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በሰሜን በኩል ሻቃ በቀለ ትልልቅ ጀብዶችን እየሰሩ እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪም የንጉሰ ነገስቱን ትዕዛዝ ተቀብለው ሻቃ በቀለ ወያን አስከትለው ወደ ደቡብ ጦር ግንባር አቀኑ፡፡በዚህም ወቅት ጀግናው ሻቃ በቀለ ወያ ታሪክ የማይረሳው ትልቅ ጀብድ ሰርተዋል፡፡ይህንንም የጀብድ ስራ ታደሰ ዘወልዴ በ1960 ቀሪን ዘወልዴ በተሰኘ መፅሀፋቸው ውስጥ ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ፤
 የጠላት ታንክ ወገንን በማጥቃቱ ደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪ በጣም ያዝኑ ነበር፡፡አንድ ቀን አምስት ታንኮች በመደዳ ሆነው ጦሩን እያጠቁ ሲመጡ ‹‹በቀለ ያንተ ብልሃት ለመቼ ሊሆነን ነው?››እያሉ ደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪ ሲያዝኑ በቀለ ዝም ብሎ ይመለክት ነበር፡፡ታንኮቹ ጠጋ ብለው በደንብ ሲታዩት በመድፍ የመጀመሪያውን አኮማተረው፤ደግሞ የኋለኛውን ደገመው፡፡እንደዚሁ በአምስት ደቂቃ ውስጥ አምስቱንም ታንኮች አቃጥሎ ሲነዱ‹‹ደጃዝማችሄደው እሳት ይሙቁ››አሏቸው፡፡ ሲሉ የወቅቱን የጀግንነት ስራቸውን በከፍተኛ አድናቆት ፅፈዋል፡፡
ደጃዝማች ገብረማሪያምና ሰራዊታቸው በደቡብ የጦር ግንባር በነበራቸው ቆይታ ሻቃ በቀለ በግንባር ቀደምነት ተሰልፈው በመግጠም፤በያዙት መድፍ የጠላትን ጦር መሳሪያ ማከማቻ አውድመዋል፡፡በዚህም ጦርነት ወቅት በሻቃ በቀለ ወያ በሚመራው ጦር ስምንት ባለውሃ ከባድ መትረየስና አስራ አራት ቀላል ድግን አልቤን መትረየስ ሲማረክ፤30 የጣሊያን መኮንኖችና ቁጥራቸው ያልታወቀ የጠላት ወታደሮች በጦሩ ሜዳ ወድቀው ነበር፡፡ከዚህም ታሪካዊ ክስተት በኋላ ከሰኔ 1 ቀን 1928 እስከ መስከረም 23 ቀን 1929 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ ጦርነት አካሄደዋል፡፡ከነዚህም መካከል፤
Ø  ከህዳር 13 እስከ 19,1929 በአለታ ወንዶ ተፈሪ ኬላ በተባለው አካባቢ
Ø  ጥር 12 ቀን  1929 አርቤጎና ላይ
Ø  ጥር 15 ቀን 1929 በዳኤላ ጭሪ አካባቢ
Ø  ጥር 19 ቀን 1929 በሂበኖ አሩሲ
Ø  መስከረም 10 ቀን 1932 ዓ.ም ሶዶ ባንቱ
Ø  ሚያዚያ 23 ቀን 1932 ዓ.ም ዝቋላ እና
Ø  የካቲት 5፤10 እና 11 ቀን 1929 በላቂ ደንበል እና በደባ ስሬ 12 ሁለት ታንኮችን በመድፋቸው በማውደም የሰሩት የጦር ሜዳ ታሪክ ዘላለም የማይረሳ ሆኖ አልፎል፡፡
ደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪ የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም ሶዶ ውስጥ ጎጌቲ ስብስቴ ገብርኤል አካባቢ በተደረገ ከባድ ውጊያ ህይወታቸው በማለፉ ሻቃ በቀለ ወያ ሙሉ ኃላፊነቱን ተረክበው ትውልድ ሀገራቸውን ከጠላት ቁጥጥር ለመታደግ ችለዋል፡፡በየካቲት ወር 1930 ዓ.ም የሶዶና ሜጫ ወሰን ላይ ሁለት ባታልዮን የጠላት ጦር ገጥመው ጀግንነታቸውንና ጥንካሬአቸውን አረጋግጠዋል፡፡በዚሁም ወር ተከታታይ ጦርነቶችን ያካሄዱ ሲሆን፤በተለይም በአገምጃ ጦርነት ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ድረስ በአይሮፕላንና በመድፍ ከታገዘው የወራሪ ጦር ጋር ያደሩጉት ጦርነት የሚዘነጋ አይደለም፡፡በዚህ ጦርነት ብዙ የሶዶ ታጋዮች ቢረግፉባቸውም፤ የማታ ማታ ድሉ የሳቸው ሆነ፡፡የጀግናውም ሻቃ በቀለ የጀብዱ ስራ ከቀን ወደ ቀን እያደገና እየጎላ በመምጣቱ፤የአገር ነጻነት የጠማው የሶዶ ጀግና ሁሉ ከጦራቸው ጋር ተሰልፎ መስዋዕትነት ለመክፈል መጉረፍ ጀመረ፡፡
ሻቃ በቀለ ወያ ትግላቸው የነፃነት ወይም የሞት መሆኑን በአንድ ወቅት የጠላት ወገን የዛቻ ደብዳቤ ሲደርሳቸው በጣም አዝነው መልሱን ከመድፍ ጋር ልከው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ከላይ ከተጠቀሱት ጦርነቶች በተጨማሪ ሌሎች ከባድ የሚባሉ ጦርነቶች አድርገው ብዙ የጣሊያን ወታደሮችንና መኮንኖችን ማርከዋል፤ገድለዋል፡፡ለትልልቅ ጀነራሎች ሞትም ምክንያት ነበሩ፡፡እንደመረጃዎቹ እውነታ ሻቃ በቀለ ወያ በሳቸው በኩል የተሰለፈው የሀበሻ ጦር ለጣሊያን መኮንኖችና ጀነራሎች ትልቅ ራስ ምታት እንደነበርና ሻቃ በቀለ የጣሊያን ወታደሮችና መሳሪያዎች ጠር እንደነበሩ ያሳያል፡፡
ጀግናው ሻቃ በቀለ ወያ ካደረጓቸው ከባድ ጦርነቶች ውስጥ አንዱ፤‹‹አቡ››በመባል በሚታወቀው ቦታ ከወሊሶና ሶዶ አገረ ገዥና የ24ኛ ብርጌድ አዛዥ ከነበሩት የጣሊያን ኮሎኔል ካዛባሳ ጋር ያደሩጉት ጦርነት ነው፡፡በዚህም ጦርነት 26 የፋሽስት መኮንኖችና 60 ወታደሮች ሲገደሉ የጦሩ መሪና የወሊሶና ሶዶ አውራጃ ገዥ የነበሩትም ኮሎኔል ካዛበሳ በዚሁ እለት በጦርነቱ ውስጥ ሞተዋል፡፡የታሪክ ፀሐፊው ታደሰ ዘወልዴ ስለዕለቱ ጦርነት ሲገልፁ፤
በ18 ካሚዮን የነበሩትን ፋሽስቶች አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨረሱአቸው፡፡ወዲያውኑ አስከሬናቸው በፍጥነት ወደነበሩበት ካሚዮን እንዲሰበሰብ ከተደረገ በኋላ ናፍጣ አርከፍክፈውና በእሳት አቀጣጥለው ሌሉቱን እንደጧፍ ሲነድ አደረ፡፡  
በማለት ምስክርነታቸውን በፅሁፍ ገልፀዋል፡፡ይህም ውጤት ጀግናውን ሻቃ በቀለ ወያን እጅግ ያኮራ ነበር፡፡የዚህ ጦርነት ድል በጠላት ወገን ላይ የፍርሃትና የስጋት ጥላ እንዲያጠላ ሲያደርግ፤በወገን በኩል ደግሞ የበለጠ ድጋፍና አክብሮት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡
ሻቃ በቀለ አምስቱንም አመት ሙሉ በየሸንተረሩና በየገደሉ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ታግለዋል፡፡የደሙላትና የቆሰሉላት አገራቸውም በአርበኞቿ ትግልና መስዋዕትነት ታሪኳ ተጠብቆና ጀግንነትዋ በአለም ታውቆ በመጨረሻ ነፃነቷን ዳግም ለማግኘት በቅታለች፡፡
ንጉሰ ነገስቱ ከስደት ከተመለሱ በኋላ ሀገራቸውን ለነጻነት ላበቁ አርበኞች ሽልማት ሰጥተው አመስግነዋል፡፡ሻቃ በቀለም ከነጻነት በኋላም ሀገራቸውን በተለያዩ ማእረጎች አገልግለዋል፡፡እነሱም፡-
1.   በ1933 በፊታውራሪነት ማዕረግ የሲዳሞ ጥብቅ አስተዳዳሪና የክብረ መንግስት የወርቅ ማዕድን ኃላፊ፤
2.   በ1933 የሁለተኛ ሬዥማን አዛዥ፤
3.   በ1934 በወለጋ የሶዩ አውራጃ ገዥ፤
4.   በ1935 በደጃዝማችነት ማዕረግ የጨቦና ጉራጌ አውራጃ ገዥ፤
5.   በ1936 የወላይታ አውራጃ ገዥ፤
6.   በ1938 በሀረር የጨርጨርና ኢሳ አውራጃ ገዥ በመሆን ሰርተዋል፡፡

 ደጃዝማች በቀለ ወያ ህይወታቸው ሲያልፍ ገና የ44 ዓመት  ጎልማሳ ነበሩ፡፡በስራ ገበታቸው ላይ ሆነው ሀገራቸውን በቅንነት ሲያገለግሉ የነበሩት ደጃዝማች ባጋጣማቸው ህመም በሀገር ውስጥ ሲታከሙ ቢቆዩም ስላልተሻላቸው ወደ ሲዊዘርላንድ ሄደው ሊታከሙ ጉዞ ላይ እያሉ ሚያዝያ 6 ቀን 1946 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡አስከሬናቸውም ሚያዚያ 10 ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ብዙ ዘመድና አዝማድ፤የመንግስት ባለስልጣኖች፤የአርበኞች ማህበር አባላት፤በግልና በዝና የሚያውቃቸው የአዲስ አበባ ህዝብ በተገኘበት በስላሴ ቤተክርስቲያን አርፏል፡፡
ንጉሰ ነገስቱ ከስደት ከተመለሱ በኋላ ለደጃዝማች በቀለ ወያ ከተሰጣቸው ሽልማት መካከል በፋሽስት ወረራ ወቅት የጣሊያን አየር ኃይል ጀነራል መኖሪያ ቤት የነበረው በአሁኑ መጠሪያው ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ውብና ትልቅ ግቢ ነው፡፡ይህም ቤት ከደጃዝማቹ ህልፈት በኋላ ቤተሰቦቻቸው የአካባቢው ህጻናት ይማሩበት ዘንድ ለትምህርት ቤትነት ሰጥተው ነበር፡፡የደጃዝማች በቀለ ወያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ብዙ ለሀገር የጠቀሙ ተማሪዎችን ያፈራ ሲሆን በተለያዩ ወቅቶችም በክፍለ ከተማዎች መካከል በተደረገ የጥያቄና መልስ ውድድር፤የፈጠራና ሳይንስ አውደ ርዕዮች እንዲሁም በተለያዩ ስብስሰባዎች ላይ እየተገኙ ሲያሸንፉና ጥሩ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን ይሰጡ እንደነበር ወረቀቶች ያስረዳሉ፡፡
ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ግን በልደታ መልሶ መገንባት ፕሮጀክት የደጃዝማች በቀለ ወያ መኖሪያ ቤትና ትምህርት ቤት ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ታሪካዊ ቤት ሙሉ ለሙሉ ፈርሷል፡፡በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበሩት መምህራንና ተማሪዎች ወደ ተለያዩ የክፍለ ከተማው ትምህርት ቤቶች ተዛውረው እንዲማሩና እንዲያስተምሩ ተደርጓል፡፡የልደታ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ልማት ቅርስ አስተዳደር አስተባባሪ የሆኑት አቶ ታደሰ ከበደ እንደሚሉት የደጃዝማች በቀለ ወያ መኖሪያ ቤት በ2002 ዓ.ም በቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ይሁን እንጂ ለመንገድ ስራ እና ለጋራ መኖሪያ ቤቶች የወጣው ንድፍ የደጃዝማቹን ታሪካዊ ቤት ከግምት አላስገባም፡፡የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና የልደታ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም አስተዳደር በጥምረት አለመስራታቸው ቅርሱን እንድናጣ አድርጎናል ያሉት አስተባባሪው ቅርሱ ሳይፈርስ በፊት የቱሪዝም ልማትና ቅርስ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
የደጃዝማች በቀለ ወያ ታሪካዊ ቤት ከፈረሰ ወዲያ የልደታ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ በክፍለ ከተማው ያሉትን ወደ 13 የሚሆኑ ቅርሶችን ለማስመስገብበ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡የደጃዝማች በቀለ ወያንና ሌሎች በአካባቢው የነበሩትን ደጃዝማቾች ታሪክ ተተኪው ትውልድ እንዲያውቀው በክፍለ ከተማው ውስጥ በሚገኙት ትምህርት ቤቶች ባሉት የሀገርህን እወቅ ክበባት በመጠቀም ለመስራት እንደታሰበም ለማወቅ ችለናል፡፡
የነበሩትን ጀግኖቻችን ትተውት የሄዱትን ቁሳዊ ቅርሶች እያፈረስን ታሪካቸውን ማሞገስ የሚመስል ነገር አይደለም፡፡ዛሬ የመኖራችን ምክንያት የነሱ ጀግንነት ነውና አሁንም በህይወት ያሉ ቅርሶችን የመጠበቅ፤ሲፈርሱ ለምን የማለት እንዲሁም ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ››እንዲሉ ያለፈውን የሀገራችንን ታሪክ የማወቅ ጉጉት ይኑረን እያልን በሌላ የለምሳሌ ፕሮግራም እስክንገናኝ ቸር ያቆየን‼‼!    


                              (ታቦር ዋሚ፤1986፤አባ ቦራ)

(ሺፈራው መንገሻ፤1993፤የሻቃ በቀለ ወያ ታሪክ)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

 ሌላ ሰው….. የሃገራችን የስነ ልቦና መጽሃፍት ጅማሬ

አራቱ መንገደኞች